የትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮው አመት ተግባራዊ በተደረገው የትምህርት ብርሀን ምዘና እንደ ሀገር ከ446 ሺህ በላይ ወጣቶችና ጎልማሶች መመዘናቸውን አስታውቋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር ጌታሁን ጋረደው የጎልማሶች ትምህርትን ከዚህ በላይ ውጤታማ ለማድረግ በክረምት የወጣቶች በጎፍቃድ አገልግሎት ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በሁሉም ክልሎች ይከናወናል ብለዋል፡፡
በዚህ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ንቅናቄ ማንበብ፣መፃፍና ማስላት የማይችሉ ወጣቶችና ጎልማሶችን የማስተማር ስራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
መፃፍና ማንበብ የሚችሉትን ጎልማሶችንም ለቀጣይ የትምህርት ብርሃን ምዘና የማዘጋጀት እንዲሁም የክህሎት ስልጠና የሚሰጥባቸውን ቦታዎች የማመቻቸት ስራ እንደሚሰራም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
የ ዲቪቪ ኢንተርናሽናል (DVV International) የምስራቅ አፍሪካ ክልላዊ ዳይሬክተር የሆኑት ፍራውካ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በጎልማሶችና መደበኛ ባለሆነ ትምህርት ዘርፍ እየሰራች ያለችውን ስራ አድንቀው በቀጣይ በስርዓት ግንባታ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን መሰረት ያደረገ የጎልማሶች ትምህርት ላይ በትኩረት አብረን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ዲቪቪ ኢንተርናሽናል (DVV International) የጀርመን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን በሀገራችን የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ዘርፍ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆን ትምህርት ዘርፍ የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና የ2014 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት እያደረገ ይገኛል፡፡
በመድረኩም ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የቢሮ ምክትል ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የጎልማሶች ትምህርት እያሰለጠኑ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከዲቪቪ ኢንተርናሽናል የተውጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡