ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰጡትን ትምህርት ጥራት እንዲመዝን እና የብቃት ማረጋገጫ እንዲሰጥ የተቋቋመው ኤጀንሲው፤ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ሳይችል ቆይቷል፡፡
በኤጀንሲው ላይ የተደረገ ጥናት፤ ተቋሙ የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉት አረጋግጧል።
የኤጀንሲው ተጠሪነት ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሆኖ መቆየቱ የቁጥጥር ሥራውን ከማዳከም ባለፈ የገለልተኝነት ችግር እንዲነሳበት ማድረጉን የኤጀንሲው የእውቅና አሰጣጥ ዳይሬክተር አብይ ደባይ ተናግረዋል።
ይህም ኤጀንሲው በአካባቢያዊና ዓለም ዐቀፍ ማህበራት አባል እንዳይሆን ማድረጉን ገልፀዋል።
ላለፉት 18 ዓመታት ሥራ ላይ የቆየው ኤጀንሲው፤ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱ ሌላው ጥናቱ በድክመት የለየው ጉዳይ ነው።
በመሆኑም ኤጀንሲው መሠል ጉድለቶቹን አርሞ በገለልተኝትና በብቃት ሥራውን እንዲከውን በአዲስ መልኩ ራሱን ችሎ በአዋጅ ይቋቋማል ተብሏል፡፡
ተቋሙ "የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ጥራት ኮሚሽን" በሚል ስያሜ እንደሚቋቋምና ተጠሪነቱም በቀጥታ ለሕዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት እንደሚሆን የተቋሙ ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ ይገልፃል።
በቀጣይ ዓመት ወደ ሥራ የሚገባው የሕዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት ረቂቅ ሕጉን እንደሚያፀድቀው ይጠበቃል። #ሸገርኤፍኤም #edunews