የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከኩረጃና ከስርቆት ነጻ ሆነው ፈተናውን መውሰድ ይኖርባቸዋል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
መስከረም 29 ቀን 2015 (ኢዜአ)የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከኩረጃና ከስርቆት ነጻ ሆነው ፈተናውን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲወስዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተፈታኞቹን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “የኢትዮጵያ የነገ ተስፋዎች የሆናችሁ ተፈታኞች ኢትዮጵያ እናንተን ስታይ ተስፋ ነው የሚታያት” ሲሉ ገልጸዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናው ለኢትዮጵያ እውነተኛ ተስፋዎች መሆናችሁን ልታሳዩበት ይገባል ብለዋል።
ወላጆች፣መምህራንና መላው ማህበረሰብ እናንተን እዚህ ለማድረስ ለዓመታት ለፍቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተፈታኞች ከኩረጃና ከስርቆት ነጻ በመሆን እንዲሁም በራስ በመተማመን ፈተናውን በመፈተን ውጤታማነታቸውን ማሳየት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ተፈታኞች የተሰጣቸውን መመሪያ በማክበርና ያለ ምንም መሸበር ፈተናቸውን መፈተን እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
“ለ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የኢትዮጵያ አምላክ ዕውቀቱን ይግለጥላችሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለመውሰድ የመጀመሪያ ዙር ተፈታኞች ከመስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ዩኒቨርስቲዎች እየገቡ ይገኛሉ።
ከመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እየገቡ ሲሆን ከ975 ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።