የዩኒቨርሲቲ መግቢያ መቁረጫ ነጥብ ይፋ ከተደረገ በኃላ ቅሬታ አለን የሚሉ ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጥያቄ እያቀረቡ/የቲክቫህ አባላትም ቅሬታቸውን ልከዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአ/አ ቅሬታ አለን የሚሉ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ዛሬ በሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ፊት ለፊት ተሰባስበው ጥያቄ እንዳቀረቡ በላኩት መልዕክት አሳውቀውናል።
ተማሪዎች ጥያቄ ?
በተማሪዎች በኩል የሚመጡት ጥያቄዎች መካከል ዋነኛው "የማለፊያ ነጥብ ይቀነስልን" የሚል ነው። ተማሪዎቹ ለዚህ ምክንያት የሚሉት በሀገሪቱ የነበረው ሁኔታ ታሳቢ ሊደረግ ይገባ ነበር የሚል ነው። ተማሪዎቹ ነባራዊ ሁኔታ እያሉ የገለፁት ፥ "በሀገሪቱ የነበረ አለመረጋጋት፣ ኮሮና፣ የትምህርት ቤት ዝግጅት እጥረት፣ የተማሪዎች አእምሮ ቀውስ" የሚሉትን ነው።
ቅሬታ አቅራቢ ተማሪዎቹ "የግል ተቋማት መግቢያ ነጥብ" እንዲቀንስልን ሲሉም ጠይቀዋል።
በተጨማሪ የሚመለከታቸው አካላት ስለፈተናው አፈታተን ቁጥጥር ይፈትሹልን ሲሉም ቅሬታ አቅርበዋል፤ ይህም የፈተና ስርቆት፣ አስተማሪ ለተማሪ መልስ መስጠቱ፣ ተማሪ መኮራረጁ፣ ስልክ ይዞ መግባቱ፣ ቸልተኝነት የነበረው ፍተሻ፣ በገንዘብ ስልክ ማስገባት፤ ኢንተርኔት አለመዘጋቱ" የሚሉት ናቸው።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከቤተሰቦቹ በርካታ የቅሬታ መልዕክት ያገኘ ቢሆንም አጠቃላይ ቅሬታ አቅራቢዎቹን /የውጤት ችግር አለብን የሚሉትን ተማሪዎችን አጠቃላይ ቁጥር ማወቅ አልተቻለም።
ተማሪዎቹ አለን ለሚሉት ጥያቄ እና ቅሬታ ምላሽ እንዲሰጡ የሚመለከታቸውን አካላት ለማግኘት ጥረት ብናደርግም ለዛሬ አልተሳካልንም።
Via TIKVAH ETHIOPIA